ጥር 27/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቻይና ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ ምርቶች ላይ የጣሉት የ10 በመቶ ታሪፍ ሥራ ላይ ከዋለ ብዙም ሳይቆይ፤ ቻይና በምላሹ በአሜሪካ የጋዝ፣ የድንጋይ ከሰል፣ የእርሻ መሳሪያዎችና በሌሎች ምርቶች ላይ ቀረጥ መጣሏን አስታውቃለች።
ትራምፕ በቻይና ምርቶች ላይ የጣሉት የ10 በመቶ ቀረጥ በዛሬው ዕለት ተግባራዊ መደረግ ይጀምራል፡፡
ይህንንም ተከትሎ ቻይና 15 በመቶ በአሜሪካ የድንጋይ ከሰል እና ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ላይ እንዲሁም 10 በመቶ የአሜሪካ ድፍድፍ ዘይት፣ የእርሻ መሳሪያዎች እና አንዳንድ አውቶሞቢሎች ላይ ቀረጥ መጣሏን ይፋ አድርጋለች።
ቻይና ከታሪፍ በተጨማሪ በግዙፉ የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ጎግል ላይ የፀረ-ሞኖፖሊ ምርመራ መከፈቷንም ማስታወቋን ሮይተርስ ዘግቧል።
ቻይና በአሜሪካ ምርቶች ላይ የጣለችው አዲስ ታሪፍ ከቀጣይ ሳምንት የካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ በዘገባው ተመላክቷል፡፡
የቻይና የአፀፋ ምላሽ ትራምፕ እና የቻይናው መሪ ዢ ጂንፒንግ ሊያደርጉት ከሚጠበቀው የስልክ ንግግር በፊት የተደረገ መሆኑም ነው የተገለጸው።
ትራምፕ በትናንትናው ዕለት ከጣሉት ታሪፍ ጋር ተያይዞ ከዢ ጂንፒንግ ጋር “ምናልባት በሚቀጥሉት 24 ሰዓታት ውስጥ” ድርድር እንደሚደረግ ገልጸው የነበረ ሲሆን፤ "ከቻይና ጋር ስምምነት ማድረግ ካልተቻለ ቀረጥ መጣል በጣም ጠቃሚ ይሆናል" ብለዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ካሸነፉ ብዙም ሳይቆይ ከካናዳ እና ሜክሲኮ ወደ ሀገራቸው በሚገቡ ምርቶች ላይ 25 በመቶ ቀረጥ መጣላቸውን ያስታወቁ ሲሆን፤ ከቻይና ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ ምርቶች የ10 በመቶ ቀረጥ እንደሚጣል አስታውቀዋል፡፡
ነገር ግን ከካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ እና የሜክሲኮ ፕሬዝዳንት ክላውዲያ ሺንባም ጋር ባደረጉት ስምምነት መሰረት፤ በዛሬው ዕለት ተግባራዊ ይደረጋል የተባለውን የታሪፍ ውሳኔ ለ30 ቀናት እንዲራዘም መደረጉን ትራምፕ አስታውቀዋል፡፡
መሪዎቹ ትራምፕ የሕገ-ወጥ ሰዎች እና የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርን ለመቆጣጠር ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት፤ የድንበር ማስከበር ሥራዎችን ለማጠናከር መስማማታቸውን ተነግሯል።
ካናዳ የተደራጁ ወንጀሎችን፣ የፈንታኒል ኮንትሮባንድ እና ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመዋጋት ከአሜሪካ ጋር በጋራ ለመስራት መስማማቷ የተገለጸ ሲሆን፣ ሜክሲኮ ደግሞ የሕገ-ወጥ ስደት እና የአደንዛዥ እፅ ዝውውርን ለመቆጣጠር 10 ሺሕ የሚጠጉ ወታደሮቿን በሁለቱ ሀገራት ድንበር ላይ እንዲሰማሩ ለማድረግ ስለመስማማታቸውም ተነግሯል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ቻይና በአሜሪካ ምርቶች ላይ የ10 እና 15 በመቶ ቀረጥ መጣሏን አስታወቀች
አሜሪካ በካናዳ እና ሜክሲኮ ላይ ጥላው የነበረውን 25 በመቶ ታሪፍ ለ30 ቀናት አራዝማለች
