ከተጫዋቾቹ እስከ ደጋፊው የሚያቧቅስ የዘመናት ባላንጣነት ያላቸው መድፈኞቹ እና ቀያይ ሰይጣኖቹ ተጠባቂውን ጦርነት
በኢምሬትስ የጦር ሜዳ አካሒደዋል።
የሠሜን ለንደን ኩራት የሆነው እና በሚካኤል አርቴታ የሚመራው አርሰናልም
በአሰልጣኝ ሮቨን አሞሪም የሚመራውን ቡድን አንገት አስደፍቶ መልሶታል።
ቀዝቀዝ ባለ ጦርነት ለ45 ደቂቃ ከተፋለሙ በኋላ ከረፍት መልስ ሞቅ ባለ ተጋድሏቸው የመድፈኞቹ የኋላ ደጀኖች አከታትለው በተኮሷቸው ሁለት ኢላማዎች ቀያይ ሰይጣኖቹን ድባቅ መምታት ችለዋል።
የመድፈኞቹ ተከላካይ ምኒስትር የሆኑት ቲምበር እና ሳሊባ የኋላ ደጀንነትን ብቻ ሳይሆን የማጥቃት ድርሻውንም በሚገባ በመውሰድ የአሞሪሙን ሰራዊት ሽንፈት አስጎንጭተውታል።
የእንግሊዙ ታሪካዊ ቡድን ማንቸስተር ዩናይትድም አርሰናልን ለመግረፍ ይቅርና ለመገላመጥ የሚያስችለውን አቅም ሳያሥመለክተን ዘጠና ደቂቃው ተገባዶ ፍልሚያው በዳኛው ፊሽካ ተጠናቋል።
በእርግጥ ቀያይ ሰይጣኖቹ መድፈኞቹን ድል ለማድረግ የሚያሥችላቸውን አቅም ካጡ እነሆ ድፍን ሶስት አመታት ሆኗቸዋል።
በትላንቱ የመድፉ መንደር ግጥሚያም በታሪክ ለአራተኛ ተከታታይ ጊዜ ሽንፈት የተጎነጩበትን ፅዋ ታቅፈው ወደ ካሪንግተን ተመልሰዋል።
ይሕ የትላንቱ የመድፈኞቹ እና የቀያይ ሰይጣኖቹ ተጠባቂ የግጥሚያ መረሃ ግብር
የቆሙ ኳሶች ልዩነት የፈጠሩበት እና የአርሰናል የቆመ ኳስ አሰልጣኝ ብልሀት የታየበት ጨዋታ ሆኖ አልፏል።
ሁለቱም ቡድኖች የማጥቃት እና የመከላከል ሽግግሮቻቸውን በተገቢ ግን ከድሮው ቀዝቀዝ ባለ ሁኔታ ከውነዋል።
ማንችስተር ዩናይትድ አደጋን ሊቀንስ በሚችልበት መልኩ ተጫውቷል።
አርሰናሎችም የዩናይትድ የመከላከል ቀጠና ላይ አደጋ የፈጠሩባቸው አጋጣሚዎች ቢኖሩም ማንቺስተር ዩናይትዶች ግን በመልሶ ማጥቃት ያን ያህል የከፋ አደጋ አልተፈጠረባቸውም።
ማንቺስተር ዩናይትድ የውሰጠኛውን የፊት መስመር የሚያገናኝ ተጫዋች አጥቶ ተስተውሏል።
ወደ ኋላ መልሶ ለመጫወትም ሆነ የውስጠኛውን የፊት መስመር የሚያገናኙ ኳሶችን ለማቀበል ሲቸገሩ ታይተዋል።
በአርሰናል በኩል ማርቲን ኦዴጋርድ እና ዴክላን ራይስ ለቡድናቸው ቁልፍ ሚናን ተወጥተዋል።
ለቀያይ ሰይጣኖቹ ደግሞ ከመከላከሉ አኳያ ቡርኖ ፈርናንዴዝ እና ማንዌል ኡጋርቴ ጥሩ እንቅስቃሴ አሳይተዋል።
አርሰናል በዚህ ግጥሚያ 13 የማዕዘን ምት ያገኙ ሲሆን ሁለቱን ወደ ግብነት መቀየር ችለዋል። ዩናይትድ በአንፃሩ ምንም የኮርና ምት ማግኘት አልቻለም።
ይሄም በጨዋታው ላይ የነበረውን የአርሰናል ከፍተኛ የማጥቃት ሂደትን የሚጠቁም ሲሆን
በሁለቱ ቡድኖች በኩል ለማጥቃት የነበረውን ፍላጎት እና አተገባበር ላይ የነበረውን የሰፋ ልዩነት የኮርናው ቁጥር ቁልጭ አድርጎ ያስቀምጠዋል።
በማጥቃቱ በኩል መድፈኞቹ በቀያይ ሰይጣኖቹ የግብ ክልል እንደፈለጉ የፈነጩ ሲሆን የዮናይትድ አጥቂዎች ግን የአርሰናልን የግብ ክልል ለመርገጥ በመድፉ ተከላካዮች ማዕቀብ ስለተጣለባቸው ብርቅ ሆኖባቸው አልፏል።
ማንችስተሮችን የጎል ያለህ ያሥባሉት የመድፉ ተከላካዮች ከመከላከል ባሻገር ኳስና መረብን በማገናኘት ምርጥ የድል ምሽትን ማሣለፍ ችለዋል።
በዩናይትድ በኩል ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ዮሮ በቀኝ የመሀል ተከላካይ በኩል በጥሩ መልኩ ሲጫወት ተስተውሏል። ለዩናይትድ ጥሩ የመሀል ተከላካይ አማራጭ ሆኖም ብቅ ማለት ችሏል።
በአጠቃላይ አርሰናሎች በተቀናጀ መልኩ ተጫውተው ጎል ለማግኘት የሚያላቸውን አጋጣሚ ለመፍጠር የተንቀሳቀሱ ቢሆንም ማንቺስተር ዩናይትድ በመከላከሉ በኩል ጥሩ ስለነበር የአርሰናሉ ሰራዊት በርካታ ጎሎችን እንዳያስቆጥሩ ገትቷቸዋል።
በአንፃሩ ደግሞ የቆመ ኳስ አጠቃቀማቸው ምን ያህል ጨዋታ ቀያሪ እንደሆነና
እንዴት በጥልቀት እንደሚሰሩበት ያሳየ ጨዋታ ሆኖ አልፏል። በማንቺስተር ዩናይትድ በኩል ከማጥቃት አኳያ ደፍሮ አደጋ የሚፈጥሩ ኳሶችን በማቀበል ረገድ ክፍተት የነበረ ሲሆን ይህም የአርሰናል ተከላካዮች በጨዋታው ላይ ብዙ ፈተና እንዳይገጥማቸው አድርጓል።
ዩናይትዶች በመከላከሉ ረገድ ከሞላ ጎደል ሩበን አሞሪምን የማያስከፋ አይነት አቋም አሳይተዋል።
ሆኖም ግን እንደ ታሪካዊ ባላንጣነታቸው ፍልሚያው እንደከዚ ቀደሙ ግጭትና ግለት ያለበት ሳይሆን ቀዝቀዝ ያለ የተዋዛ ጦርነት ነበር ማለት ይቻላል።
በኔዘርላንዳዊው ኢንተርናሽናል ቲምበር እና በፈረንሳዊው እንቁ ዊሊያም ሳሊባ የድል ጎዳናውን ያስቀጠለው መድፈኛው ሊቨርፑልን ከስር ቆሞ እያየ የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫውን ያልማል።
ለሁለት አስርት አመታት ያላነሳውንና ባለፉት ሁለት አመታት በአሳዛኝ ሁኔታ በሌላኛው የማንችስተር ክለብ በሆነው ሲቲ የተነጠቀው አርሰናል
በዚህ አመት ደግሞ ሌላ ስጋት የሆነ ቡድን ገጥሞታል።
የመርሲሳይዱ ክለብ ሊቨርፑል!
ሊቨርፑል ሊጉን በ7 ነጥቦች እርቆ እየመራ ሲሆን ይሔው የሰሜን ለንደኑ አርሰናል እና የምእራብ ለንደኑ ቸልሲ አንገቱ ስር እየተነፈሱ ይገኛሉ።
ተጠባቂው የባላንጣዎች ፍልሚያ በመድፈኞቹ አሸናፊነት ተጠናቋል።
ቀያይ ሰይጣኖቹ 2 ግቦችን አስተናግደው ወደካሪንግተን ተመልሰዋል።