ጥር 2/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) አዋሽ ባንክ በቀጣይ ሦስት ዓመታት የባንኩ የተከፈለ ካፒታል ወደ 55 ቢሊዮን ብር ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቋል።
አዋሽ ባንክ እና አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች የ30ኛ ዓመት የምሰረታ በዓል በትላንትናው ዕለት የተካሄደ ሲሆን፤ ለተከታታይ ሦስት ወራት ሲካሄድ የቆየዉ የእህት ኩባንያዎቹ የምስረታ በዓል መርሃ ግብርም መጠናቀቁ ተገልጿል፡፡
ባንኩ ይህን አስመልክቶ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደገለጸው የአዋሽ ባንክ ተቀማጭ ገንዘብ 273 ቢሊዮን ብር ሲሆን፤ አጠቃይ የብድር መጠን ከብር 203 ቢሊዮን በላይ መድረሱን ጠቁሟል።
የባንኩ ደንበኞች ብዛት ከ13 ሚሊየን በላይ ሲሆን፤ 20 ሺሕ ሠራተኞች እንዳሉት ተገልጿል።
አዋሽ ኢንሸራንስ በ456 መስራች ባለ አክሲኖዎች በ4 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር ካፒታል የተመሰረተ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ በቅርቡ የራሱን ሕንፃ ለመገንባት እቅድ ስለመያዙም ተነግሯል፡፡
አዋሽ ኢንሹራንስ ሲመሰርት በ12 ሠራተኞች የተጀመረ እንደነበርና በአሁኑ ወቅት የሠራተኞቹ ቁጥር 800 መድረሱ ተገልጿል።
ኩባንያው በ2024 አጠቃላይ ሀብቱ 7 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር መድረሱም በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡