ሰኔ 23/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በፓኪስታን አንድ ሳምንት ለሚጠጋ ተከታታይ ቀናት የጣለው ከባድ ዝናብ ባስከተለው የጎርፍ አደጋ ምክንያት፤ ቢያንስ 46 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው የሀገሪቱ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

በሀገሪቷ ካለፈው ሳምንት ማክሰኞ ጀምሮ ያልተለመደ ኃይለኛ ዝናብ መጣሉን ተከትሎ፤ በከይበር ፓክቱንክዋ ግዛት 22 ሰዎች፣ በምስራቅ ፑንጃብ ግዛት 13 ሰዎች፣ በደቡባዊ ሲንድ ግዛት ሰባት ሰዎች እንዲሁም፤ በደቡብ ምዕራብ ባሎቺስታን ግዛት አራት ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉን የብሄራዊ የአደጋ አስተዳደር ባለስልጣን እና የክልል የድንገተኛ አደጋ ባለስልጣናት ተናግረዋል።

Post image

ከፍተኛው የሟቾች ቁጥር የተመዘገበው ፓኪስታንን ከአፍጋኒስታን ጋር በሚያዋስነው በከይበር ፓክቱንክዋ ግዛት ሲሆን፤ ሕይወታቸው ካለፈው 22 ሰዎች መካከል 10 ሕጻናት እንደሚገኙበት ተዘግቧ።

የፓኪስታን የሚቲዎሮሎጂ ዲፓርትመንት ምክትል ዳይሬክተር ኢርፋን ቪርክ፤ "በበልግ ዝናብ ከመደበኛ በላይ ዝናብ እየጠበቅን ነው፡፡ እናም ለሚመለከታቸው ባለስልጣናት ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል" ሲሉ መናገራቸው አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

Post image

ይህ ከባድ ዝናብ እና የጎርፍ አደጋ አደጋ ቢያንስ እስከ ቅዳሜ ድረስ ከፍተኛ እንደሚሆንም ቅድመ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

ባለፈው ሳምንት አርብ ዕለት ሕይወታቸውን ካለፉት ሰዎች መካከል ከ17 ቤተሰብ የተውጣጡ 13 ቱሪስቶች እንደሚገኙበት የገለጹት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ የተቀሩት አራት የቤተሰብ አባላት በሰሜን ምዕራብ ኸይበር ፓክቱንክዋ ግዛት በጎርፍ ከተጥለቀለቀው የስዋት ወንዝ ውስጥ መታደግ መቻሉን አስታውቀዋል።

Post image

በፓኪስታን እ.ኤ.አ በ2022 አስከፊ በሆነ የጎርፍ መጥለቅለቅ ተመታ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፤ የሀገሪቱን አንድ ሦስተኛ ባጥለቀለቀው የጎርፍ አደጋ 1 ሺሕ 737 ሰዎች ሕይወቸው ሲያልፍ፤ አደጋው በሀገሪቱ ላይ ሰፊ ውድመት አስከትሏል።

ይህም የዚህ ሳምንት አደጋ ያንን "አስከፊ ሁኔታ" እንዳይደግም ትንበያ ሰጪዎች አስጠንቅቀዋል።

ፓኪስታን ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ ተጋላጭ ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ ስትሆን፤ 240 ሚሊዮን ነዋሪዎቿም ተደጋጋሚ የአየር ጠባይ ለውጥ አደጋዎች እያጋጠማቸው ይገኛል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ