ታሕሳስ 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ታሕሳስ 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የተሾሙት ከንቲባ አቶ ብርሃነ ገብረየሱስ በጊዜያዊነት ወደ ቢሯቸው መግባታቸውን በሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የክልሉ ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት ለአሐዱ አስታውቋል፡፡

በደብረፅዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው ህወሓት በዋነኝነት በሚቆጣጠረው የመቐለ ከተማ ምክር ቤት፤ ዶክተር ረዳኢ በርሃ የመቀሌ ከተማ ከንቲባ ሆነው እንዲሰሩ ባለፈው ጥቅምት ወር አጽድቆ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

ይህንንም የተቃወመው የትግራይ ግዜያዊ አስተዳደር ደግሞ፤ አቶ ብርሃነ ገብረየሱስ የመቀሌ ከንቲባ ሆነው እንዲሰሩ ባለፈው ሕዳር 22 ቀን 2017 ዓ.ም ሹመት ሰጥቶ ነበር።

ከዚህ ጋር በተያያዘ አሐዱ "ጉዳዩ ከምን ደረሰ?" ሲል የትግራይ ቅርጫፍ እምባ ጠባቂ ተቋምን ጠይቋል፡፡

Post image

ይህንንም ተከትሎ ግልፅ የአስተዳደር ክፍተት እየታየ መቆየቱን፤ የተቋሙ ኃላፊ አቶ ፀሀዬ እምባዬ ለአሐዱ በሰጡት ምላሽ ገልጸዋል፡፡

ቅርጫፍ ጽህፈት ቤቱ በዚህ አንድ ወራት ግዜ ውስጥ ሕዝቡ የት መሄድ እንዳለበት ጭምር ግራ ከመጋባት በተጨማሪ አገልግሎት ለማግኘት መቸገሩንም የገለጹት ኃላፊው፤ በአሁን ሰዓት ግን ችግሩ ተፈቶ በጊዜያዊ አስተዳደሩ የተሾሙት ከንቲባ አቶ ብርሃነ ገብረየሱስ ወደ ቢሯቸዉ መግባታቸውን ተናግረዋል።

በመቀሌ የነበረው ችግር በጊዜያዊነት እንደተፈታ የገለጹት አቶ ፀሀዬ፤ ይህ ችግር በአዲግራት እና በሌሎች የትግራይ ከተሞች ጭምር መኖሩንም ገልጸዋል፡፡

ቅርጫፍ ጽህፈት ቤቱ ሕዝቡ በብዙ መንገድ መቸገሩን ቢገልፅም፤ ፍርሃት በመኖሩ ቅሬታ ለማቅረብ የመጣ የከተማ ነዋሪ አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡

ይህንን በመቃወም በሳለፍነው ሳምንት በመቀሌ ከተማ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ማህበረሰብ ሰላማዊ ሰልፍ በመውጣት በጊዜያዊ አስተዳደሩ የተሾመ ከንቲባ ወደ ቢሮ እንዲገባ መጠየቁ የሚታወስ ነው፡፡

በህወሓት እና በጊዜያዊ አስተዳደር መካከል የተፈጠረዉን ውዝግብ ተከትሎ፤ የመቐለ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ፅሕፈት ቤት ከታሸገ አንድ ወር መቆየቱ ይታወሳል።