ይህ የተነገረው ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በማስመልከት በሀዋሳ ከተማ በተካሄደው የፓናል ውይይት ላይ ነው።
አለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን ዛሬ ታህሳስ 3 በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ33ኛ ተከብሮ ይውላል። በኢትዮጵያ ደግሞ ለ32ኛ ጊዜ "የአካል ጉዳተኞችን የመሪነት ሚና በማጉላት አካታችና ዘላቂ ልማትን እናረጋግጥ!" በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ይገኛል፡፡
በሀዋሳ ከተማ ቀኑ በማስመልከት በተካሄደው የፓናል ውይይት ላይም ከጤና፣ ከትምህርት፣ ከማህበራዊ ድጋፎች፣ ማህበራትን ከማደራጀት፣ አጋዥ መሣሪያዎችን ከማቅረብ፣ ማህበራዊ ተሀድሶ ተቋማትን ከማስፋፋት፣ አስገዳጅ ሕግ ማዕቀፍ ከማዘጋጀት አንፃር የተሰሩ ሥራዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በውይይቱ አንደ ተግዳሮት ከተነሱት መካከል፤ ተደራሽ አለመሆን፣ የአካል ጉዳተኞች አሁናዊ ዳታ አለመኖር፣ የመንገዶችና ሕንፃዎች ግንባታ አካል ጉዳተኞችን በበቂ ሁኔታ ያገናዘበ አለመሆን እንዲሁም የአካል ጉዳተኞች የተጠቃለለ ሕግ አለመፅደቅ እንደሚገኙበት ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን እ.ኤ.አ በ1992 በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ በተወሰነ ውሳኔ መሰረት መከበር የጀመረ ሲሆን፤ ዕለቱ የአካል ጉዳተኞችን መብትና ደህንነት በሁሉም ዘርፎች ለማስከበር እንዲሁም የፖለቲካ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ እና ግንዛቤን ለማሳደግ ታስቦ ይከበራል።
በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ከ1 ቢሊዮን የሚበልጡ ሰዎች የአካል ጉዳት እንዳለባቸው የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ያመላከተ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ ከ100 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ አካል ጉዳተኞች ሕጻናት መሆናቸውን ገልጿል፡፡
እንዲሁም አካል ጉዳተኛ የሆኑ ሕጻናት ላይ የሚደርሰው ጥቃት የአካል ጉዳት፤ ከሌለባቸው ሕጻናት በአራት እጥፍ እንደሚበልጥም በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
በኢትዮጵያ ከ17 ነጥብ 6 በመቶ በላይ ሰዎች የአካል ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተገለጸ
ሕዳር 24/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ ከ17 ነጥብ 6 በመቶ በላይ ሰዎች የአካል ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የአለም ጤና ድርጅትና አለም ባንክ ያጠናው ጥናት መጠቆሙ ተገልጿል፡፡