ታሕሳስ 25/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በሰላም ዙሪያ ውይይት ለማድረግ በተደጋጋሚ ጥሪ ቢናደርግም በመንግሥት በኩል ቁርጠኝነት ባለመኖሩ ሰሚ አጥተናል ሲሉ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) እና ነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡
"ኢትዮጵያ በልጆቿ ትታረቅ" በሚል ከተለያዩ ፓርቲዎች ጋር በጋራ በመሆን የሰላም ጥሪዎችን በተደጋጋሚ ሲያደርጉ እንደነበረ የገለጹት ፓርቲዎቹ፤ ከመንግሥት እና ከማህበረሰቡ በጋራ በመሆን ውይይት ለማድረግ ያደረጉት ጥሪ ሰሚ ማጣቱን ተናግረዋል፡፡
የነጻነት እና እኩልነት የአደረጃጀትና የአቅም ግንባታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙባረክ ረሺድ፤ "ውይይቶችን ለማካሄድ፣ ታጣቂ ኃይሎችን ለማግኘት እና ለማወያየት የቀረበ ጥሪ ባለመኖሩ እንዲሁም፤ በመንግሥት በኩል የሰላም ውይይት ቢፈልግም በፋይናንስ በኩል ግን ቁርጠኝነት ያለው አካሄድ የለም" ሲሉ ገልጸዋል፡፡
"በተጨማሪም 'አንዳንድ የታጠቁ ሃይሎች ወደ ሰላም እየገቡ ነው' ቢባልም፤ ዘላቂ ሰላም ግን እየመጣ አይደለም" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
"መንግሥት ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እና ዘላቂ ሰላም ለመምጣት ካሰበ፤ ብቸኛው አማራጭ ሰፊ የሆነ የሰላም ውይይቶችን ማካሄድ እና አሰራር መዘርጋት ነው" ሲሉ አቶ ሙባረክ ገልጸዋል፡፡
የኢህአፓ የአዲስ አበባ ሰብሳቢ አቶ አበበ አካሉ በበኩላቸው፤ በግልም ሆነ በጋራ ከሚሰሩ ፓርቲዎች ጋራ በመሆን 'የሰላም ውይይት ይደረግ' የሚል ጥሪ በተደጋጋሚ ማድረጋቸውን ገልጸው፤ ሆኖም የሚያደርጉትን የሰላም ጥሪ መንግሥት ችላ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም "ፓርቲዎች የሚያቀርቡትን የሰላም ጥሪ መንግሥት በሥሩ ባሉ የመገኛኛ ብዙሃን አማራጮች ተደራሽ ባለማድረጉ የሰላም ጥሪው ተቀባይነት እንዲያጣ አድርጓል" ብለዋል፡፡
አክለውም፤ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር የሰላም ውይይት ግዴታ መሆኑን አሳስበዋል፡፡
ፓርቲዎቹ ስለ ሰላም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ በመሆን ውይይት ለማድረግ ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸው፤ ዘላቂ ሰላም እንዲስፈን ማንኛውም አካል የድርሻውን ሊወጣ መንግሥትም ቁርጠኛ ሊሆን እንደሚጋባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡