ጥር 2/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ በዓመት ውስጥ 2 ሚኒዮን 200 ሺሕ የሚደርሱ የደንብ ጥሰቶች በአሽከርካሪዎች እንደሚፈጸሙ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን አስታውቋል።

ደንብን በሚተላለፉ አሽከርካሪዎች ሳቢያም ከፍተኛ የሆነ አደጋ እንደሚከሰትና ለትራፊክ እንቅስቃሴም ችግር የሚፈጥር መሆኑን የባለስልጣን መስሪያቤቱ ም/ ዋና ዳይሬክተር ኤልያስ ዘርጋው ለአሐዱ ገልጸዋል።

ከደንብ ጥሰት አንፃር ለሰው ሕይወትና ለንብረት ውድመት ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር መሆኑን የገለጹት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ ይህም በመዲናዋ በስፋት የሚስተዋል የደንብ ጥሰት እንደሆነ ጠቁመዋል።

ከፍጥነት ወሰን በላይ ከማሽከርከር በተጨማሪ 52 በመቶ የሚሆኑ አሽከርካሪዎች ጠጥቶ በማሽከርከርና ለአደጋ ተጋላጭ የሚያደርጉ ድርጊቶችን እንደሚፈፅሙ ገልጸዋል።

የቅርብ ጊዜ መረጃዎች እንደሚያሳዩትም በመዲናዋ ውስጥ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሚደርሱ የተመዘገቡ ተሽከርካሪዎች ሲገኙ፤ 700 ሺሕ የሚሆኑት ደግሞ በቋሚነት የተመዘገቡ ናቸው ብለዋል።

በመሆኑም ከከተማዋ ውጪ የሚኖሩ ተሽከርካሪዎች ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በከተማዋ ውስጥ እየገቡ የሚወጡ በመሆናቸው ትላልቅ ችግሮች መኖራቸውን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አክለው ገልጸዋል።