የምጣኔ ሃብት ባለሙያው እንዳይላሉ ሰለሞን እንደተናገሩት ከሆነ፤ መንግሥት ከበጀተው ተጨማሪ በጀት ተመላሽ ገቢ ሊያሰገኝ የሚችል ኢንቨስትመንት ላይ ያዋለው የብር መጠን አነስተኛ በመሆኑ የዋጋ ግሽበቱን ሊያባብሰው ይችላል፡፡
ባለሙያው አክለውም፤ መንግሥት ደሞዝተኛውን በደምወዝ ጭማሪ ብቻ ሳይሆን በአገልግሎትም ሊደግፈው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
"በተጨማሪም መንግሥት ተጨማሪ በጀት ሲበጅት ከታክስ ገቢ ለማግኘት አቅዶ ከሆነ፤ ይህ የማህበረሰቡን አቅም የሚያዳክም ነዉ" ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል።
የቢዝነስና ኢንቨስትመንት አማካሪው ከፈለኝ ሃይሉ በበኩላቸው፤ የተደረገው የበጀት ጭማሪን በዶላር ቢሰላ ካለፈው ዓመት ሊያንስ እንደሚችል ገልጸው፤ "በተደረገው ጭማሪ ሳቢያ መንግሥት በሚሰበስበው ግብር ምክንያት ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ላይ ጫና ያሳድራል" ብለዋል፡፡
ባለሙያው አክለውም፤ ኢኮኖሚው የወጣውን ያክል ገንዘብ የመሰብሰብ አቅም እንዳለውም ሊጠና እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም የበጀት ጭማሪ መደረጉ አሉታዊ ብቻ ሳይሆን አዎንታዊ ተጽዕኖ እንዳለው የተናገሩ ሲሆን፤ "የበጀት ጭማሪ መኖሩ የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶች እንዲስፋፉ ያደርጋል" ብለዋል፡፡
የቢዝነስና ኢንቨስትመንት ባለሙያው አክለውም፤ "ተጨማሪ በጀት መፅደቁ የተለያዩ የድንገተኛ አደጋዎችን በፍጥነት ለመመለስ እንዲሁም የተለያዩ የመህበረሰቡን ጥያቄዎች ባስቸኳይ ሊመልስ ይችላል" ሲሉ ገልጸዋል።
ባለሙያዎቹ የበጀት ጭማሪ መደረጉ የዋጋ ንረቱን እንደሚያባብስ በመግለጽ፤ "የተሻለ አተገባበር ተፈፃሚ የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት እንዲሁም ድንገተኛ አደጋ ቢፈጠር ለመቆጣጠር ይጠቅማል" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት ሕዳር 17 ቀን 2017 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለ2017 በጀት ዓመት የቀረበለትን የ582 ቢሊየን ብር የበጀት ጭማሪ በአብላጫ ድምጽ በ3 ተቃውሞ እና በአምስት ድምጸ ታቅቦ ማፅደቁ ይታወሳል። በዚህም መሠረት የ2017 አጠቃላይ በጀት 1 ነጥብ 55 ትሪሊዮን ብር ደርሷል።
በመንግሥት የተደረገው የበጀት ጭማሪ የዋጋ ግሽበት ሊያስከትል እንደሚችል የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ተናገሩ
ሕዳር 23/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሚንስትሮች ምክር ቤት የተላከለትን ተጨማሪ 582 ቢልዮን ብር በጀት ማጽደቁ፤ ማህበረሰቡ ላይ አሉታዊ ጫና ሊፈጥር እንደሚችል ተነግሯል፡፡