ጥር 2/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአሜሪካ ደቡብ ካሊፎርኒያ ግዛት በምትገኘው ሎስ አንጀለስ በተከሰተው ሰደድ እሳት ምክንያት ቢያንስ የ10 ሰዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ በሺሕዎች የሚቆተሩ ሕንፃዎች መውደማቸው ተገልጿል፡፡

የሎስ አንጀለስ ባለስልጣናት ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ በሰደድ እሳቱ ምክንያት፤ ከ10 ሺሕ በላይ ሕንፃዎች፣ መኖሪያ ቤቶች እንዲሁም በርካታ መሰረተ ልማቶች መውደማቸውን አስታውቀዋል።

በከፍተኛ ደረጃ እየተዛመተ በሚገኘው ሰደድ እሳት የሚያደርሰውን ጁዳት ለመቀነስ ከ180 ሺሕ በላይ የሎስ አንጀለስ አካባቢ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ የታዘዙ ሲሆን፤ ከ1.6 ሚሊዮን በላይ ቤቶች የኤክትሪክ ሃይል አቅርቦት አጥተዋል ተብሏል፡፡

Post image

በተጨማሪም አስከፊ ነው የተባለለት ሰደድ እሳት ከትናንት ማምሻውን ጀምሮ ወደ ሆሊውድ ኮረብታዎች የተስፋፋ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ በሎስ አንጀለስ ፓሲፊክ ፓሊሴድስ ወይንም በርካታ የአሜሪካን ዝነኞች በሚኖሩበት አካባቢ የተከሰተው ሰደድ እሳት በበርካታ ሚሊዮን ዶላሮች የተገዙና የተሰሩ የዝነኞችን ቤቶች ማውደሙም ተነግሯል፡፡

ይህንንም ተከትሎ በስፍራው የሚኖሩ ዝነኞች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ መደረጉ ተመላክቷል፡፡

Post image

በሰደድ እሳቱ ምክንያት እስከ የደረሰው የኢኮኖሚ ጉዳት ከ137 እስከ 150 ቢሊየን ዶላር በላይ እንደሚገመት አኩ ዌዘር የተባለው የግል የትንበያ ተቋም ግምቱን አስቀምጧል፡፡

ይህን አስከፊ አደጋ እንደ አጋጣሚ በመጠቀም ዘረፋ ሲፈጽሙ ነበር የተባሉ 20 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

በተጨማሪም በእሳት ማጥፋት ሥራ ላይ የነበረች የእሳት አደጋ አውሮፕላን ከድሮን ጋር መጋጨቷን እና በዚህ አደጋ ጉዳት አለመድረሱም ተገልጿል፡፡

Post image

በአካባቢው ያለው ደረቅ ንፋሳማ አየር እሳቱ በፍጥነት እንዲስፋፋና ለመቆጣጠር አዳጋች እንዲሆን ያደረገው ሲሆን፤ ሰደድ እሳቱ ወደ ሌሎች አካባቢዎች የመዛመት እድሉ ከፍተኛ መሆኑን እና የሟቾች ቁጥርም ከዚህ በላይ ሊሆን እንደሚችል ተነግሯል፡፡

አደጋውን ተከትሎ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን የሰደድ እሳቱን መዛመት ለመዋጋት ለሚያስፈልገው ሥራ የሚውል የገንዘብ እና ሌሎች ርዳታዎች ለካሊፎርኒያ ክፍለ ግዛት ለመልቀቅ የሚያስችል የፌደራል የአደጋ ጊዜ ዐዋጅ አጽድቀዋል።

ባይደን “በቀጣዩ ቀናት ውስጥ ሙሉ ትኩረታቸውን የፌዴራል መንግሥቱ ለሚሰጠው ጠቅላላ ምላሽ አመራር ለመስጠት” ወደ ጣሊያን ሊያደርጉት የነበረውን ጉዞ መሰረዛቸውን ዋይት ሀውስ ረቡዕ ዕለት አስታውቋል።

Post image

ፕሬዝዳንቱ አክለውም "ሰደድ እሳቱን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር፣ አካባቢውን መልሶ የመገንባቱ ጥረት መስመሩን እና ብሎም ወደ ቀድሞው የተረጋጋ ሁኔታ መመለሱን እስክናረጋገጥ ድረስ አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ተዘጋጅተናል።" ያሉ ሲሆን፤ አደጋውን የመቆጣጠር እና ከጉዳቱ መልሶ የማገገሙ ሥራ ብዙ ጊዜ እንደሚወስድ አመላክተዋል፡፡