ጥር 3/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ “ቃሊቲ አካባቢ” ተብሎ በሚጠራው የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ አካባቢ ባለ 'ሰፊ መጋዘን' ውስጥ፤ ከጎዳና ላይ የተነሱ በርካታ ሰዎች መኖራቸውንና ይህ ሰዎችን የመያዝና ወደ ማቆያ ማዕከል የማስገባት ድርጊት አሁንም መቀጠሉን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታውቋል፡፡
ኮሚሽኑ በሚያዝያ 27 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ በጎዳና ላይ ያሉ ሕፃናት በጅምላ ተይዘው የሚቆዩበትን ሁኔታ በተመለከተ መግለጫ ማውጣቱ አስታውሷል፡፡
እንዲሁም መስከረም 8 ቀን 2016 ዓ.ም. በሸገር ከተማ ገላን ክፍለ ከተማ ሲዳ አዋሽ ወረዳ በሚገኘው ማቆያ ማዕከል ተይዘው የነበሩ ውሎና አዳራቸውን በጎዳና ያደረጉ ሰዎችን (በተለምዶ አጠራር ‘‘ጎዳና ተዳዳሪዎች’’ ተብለው የሚታወቁ) ሁኔታ አስመልክቶ ክትትል በማድረግ የተለዩ ክፍተቶችን እና ምክረ ሐሳቦችን የያዘ መግለጫ ማውጣቱንም አመላክቷል።
ኢሰመኮ በትናንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ በታሕሣሥ ወር 2017 ዓ.ም. 'አደረግኩ' ባላቸው ክትትሎች መሠረት "ቃሊቲ አካባቢ በሚገኘው ማቆያ ከጎዳና ላይ የተነሱ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን የገለጸ ሲሆን፥ ወደ ማቆያው ከገቡት ሰዎች መካከል በማዕከሉ ከመቆየት እና የእርሻ ሥራ ከመሥራት እንዲመርጡ በማድረግ፤ የእርሻ ሥራ ለመሥራት የመረጡ ሰዎች በተለያዩ አካባቢዎች ወደሚገኙ እርሻ ጣቢያዎች ተወስደው እንዲሠሩ እንደሚደረግ ለመገንዘብ መቻሉን ገልጿል።
ይህም የግለሰቦቹን የነጻነት መብት ጨምሮ ሌሎች መሠረታዊ የሰብአዊ መብቶቻቸውን የሚጥስ መሆኑንም አስታውቋል።
ኮሚሽኑ አክሎም፤ "በአዲስ አበባ ከተማ የሚከበሩ ሕዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላት፣ የሚደረጉ ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ጉባኤዎች እንዲሁም ከሌሎች ተመሳሳይ ኹነቶች ጋር በተያያዘ ውሎና አዳራቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ሰዎችን በኃይል በማንሳት በአንድ ስፍራ እንዲቆዩ የማድረግ አሠራር እንዲቆም፤ ወደመጡባቸው አካባቢዎች የመመለስ እና የመልሶ ማቋቋም ሥራዎች ሰብአዊ መብቶቻቸውን ባከበረ መልኩ ማከናወን እንደሚገባ እና ችግሩ ሁሉ አቀፍ የፖሊሲ ምላሽ የሚያስፈልገው መሆኑን በተለያዩ ጊዜያት በተካሄዱ የኢሰመኮ ክትትሎች መጠቆሙን አስታውቋል፡፡
ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ከሚያደርገው ውትወታ ጎን ለጎን የነጻነት መብትን ከማክበር እና ከማስከበር አኳያ እንዲሁም፤ በጊዜያዊ ማቆያ ማዕከሉ ከንጽሕና እና ከጤና አጠባበቅ ጋር በተያያዘ በሰዎች ሕይወትና ጤና ላይ አደጋ የሚጥሉ ሁኔታዎች እንዳይፈጠሩ፤ ኢሰመኮ ከአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር ውይይቶችን በማድረግ ጉዳዩን በመከታተል ላይ እንደሚገኝም ገልጿል፡፡